ሀገሬ ቲቪ

በአጋዘን የተገደለው ወታደር

የፓራጓይ ወታደር በፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግስት በአጋዘን ጥቃት ደርሶበት ሞተ። የ42 አመቱ ሳጅን ቪክቶር ኢሳሲ በሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ግቢ አትክልት ስፍራ ውስጥ በአጋዘኖች ጥቃት ደርሶበት ነው ለሞት ያበቃው። እነዚህ አጋዘኖች በሀገሬው የተፈጠሩ ሳይሆኑ በዋና ከተማዋ አሱንሲዮን አቅራቢያ ላለው ቤተመንግስት በስጦታ የተበረከቱ ናቸው። የትውልድ ቀያቸው ህንድ ነበር ነው ያሉት የሀገሪቱ የዱር እንስሳት ባለስልጣን አንድ ኃላፊ። ጥቃቱ ከመድረሱ በፊት ወታደሩ እንስሳቱ ወዳሉበት ቦታ ሲገባ እና እንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ በደህንነት መጠበቂያ ካሜራ ውስጥ ታይቷል። ወታደሩ ጥቃቱ ከደረሰበት በኋላ ወደ ወታደራዊ ሆስፒታል ቢወሰድም ህይወቱን ማትረፍ ሳይቻል ቀርቷል። ጥቃቱ በደረሰበት ሰዓት ወታደሩ በመደበኛ የጥበቃ ስራው ላይ እንደነበር የእግረኛ ጦር ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ማሪዮ አብዶ ቤኒቴዝ ቤተመንግስት 10 ሄክታር የሚሸፍን ሲሆን በውስጡም በርካታ የእንስሳት እና አራዊቶች ይገኛሉ።

በሀገሬ ቲቪ
2022-01-05