ሀገሬ ቲቪ

ያለስምምነት የተበተነው የአውሮፓ ኀብረት ጉባዔ

የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ተጸዕኖ ለበርካታ ሀገራት የተረፈ እንደኾነ የሚታወቅ ነው። ሩሲያ በተለያዩ ምክንያቶች ለሀገራት የምትሸጠውን ነዳጅ ማቋረጧን ተከትሎ በተለይም ከሩሲያ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ሲሸምቱ የነበሩ ሀገራት ከባድ ቀውስ ውስጥ ገብተዋል።

በነዳጅ ዕጥረት እየታመሱ የሚገኙት አውሮፓውያን በጉዳዩ ላይ ውይይት ለማድረግ የአውሮፓ ኀብረት መሪዎች በብራሰልስ ተገናኝተው ነበር። በውይይታቸው የጋዝ ዋጋ ተመንን እነሱ ባሰቡት ዋጋ ለማስቀመጥ በሚለው ጉዳይ ውሳኔ ሊያደርጉ ቢያስቡም ይህ መኾን አለበት ማለት ሳይችሉ ቀርተዋል።

የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳነት ኡሩሱላ ቮንዴር ሌየን ዛሬ ጠዋት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "አሁን የኃይል ዋጋ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት በጣም ጥሩ እና ጠንካራ ፍኖተካርታ አለን ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል ።

ይሁን እንጂ ባለምስማማት የተጠናቀቀው የአውሮፓ ኀብረት የመሪዎች ጉባዔ በድጋሜ መቼ ሊካሔድ ይችላል የሚለው እስካሁን አልታወቀም። ነገር ግን የሀገራቱ የኃይል ሚኒስትሮች የዛሬ ሳምንት ውይይት ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

“እንደ አውሮፓው ሶስት ግቦችን ለማሳካት ጠንካራና የጋራ ቁርጠኝነት አለ” ሲሉ የአውሮፓ ካውንስል ፕሬዝዳንት ቻርለስ ሚካዔል ተናግረዋል።

የኃይል ዋጋ መቀነስ፣ የአቅርቦት ዋስትና ማረጋገጥና በዚህ ላይ ያለውን ፍላጎት ለመቀነስ የሚሉ ግቦችን ይዘናል ይህንንም ለማሳካት እንሰራለን ማለታቸውን አልጀዚራ አስነብቧል።

ከሩሲያ አሁንም ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ እያስገቡ ያሉ ሀገራት የዋጋ ተመኑ ላይ ሳይስማሙ ቀርተዋል። ምክንያቱም አሁን ላይ እያስገቡ ያሉትን የኃይል ምንጭ ከነጭራሹ ሩሲያ እንዳትከለክላቸው በመስጋት።

የሀንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኾርባን በጉዳዩ ላይ በቲውተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ጉዳዩ መጠጥ ቤት ሔዶ ቢራ ከጠጡ በኋላ ለአስተናጋጁ የቢራውን ግማሽ ዋጋ ልክፈላችሁ እንደማለት ነው ብለዋል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-10-21