ሀገሬ ቲቪ

የንግድ ፈቃድና እደሳ ክፍያን በቴሌብር መክፈል ተጀመረ

የንግዱ ማህበረሰብ ከንግድ ፈቃድ፣ ምዝገባና ስያሜ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው የአገልግሎት ክፍያዎችን ያለምንም ውጣ ውረድ በቴሌብር መክፈል ይችላሉ ተባለ።

ኢትዮ ቴሌኮም እና የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ይህን የዲጂታል ክፍያ ለማሳለጥ የሚረዳ ስምምነትን አድርገዋል።

አገልግሎት ላይ ከዋለ ወደ 18 ወር የተጠጋው የቴሌብር የዲጂታል የክፍያ መንገድ እስካሁን 24.9 ሚሊዮን ደንበኞችን በማፍራት ከ102 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ተንቀሳቅሶበታል።

የንግድ እና ቀጠናቂ ትሥሥር ሚኒስቴርም ደንበኞቹ አዲስ ንግድ ፈቃድ ሲያወጡ፣ ሲያድሱ፣ ምትክ ሲወስዱ፣አዲስ የንግድ ስም ሲሰይሙ፣ ውል ሲያቋርጡ እና ሌሎች የአገልግሎት ክፍያዎችን ሲፈጽሙ ከዚህ በኋላ በቴሌብር ማድረግ ይችላሉ ተብሏል።

ኢትሬድ የተሰኘ ከሰው ንክኪ ነጻ የኾነ የአገልግሎት ክፍያ ሥርዓት ቢጀመርም ከተቋማት ጋር ባለመዋሀዱ እንደታሰበው ውጤታ መኾን እንዳልቻለ የንግድ እና ቀጠናቂ ትሥሥር ሚኒስትር የኾኑት አቶ ገ/መስቀል ጫላ ተናግረዋል።

አሁን ላይ የቴሌብር የዲጂታል ክፍያ ከ ኢትሬድ ጋር በማቀናጀት ለተጠቃሚው እንዲደርስ መደረጉ 2.7 ሚሊዮን ለሚጠጋው የንግዱ ማኀበረሰብ ትልቅ እፎይታን እንደሚሰጥ አቶ ገ/መስቀል ጫላ ተናግረዋል።

ይኸው የክፍያ ሥርዓት ወደ ፊት አስፈላጊ እና መሠረታዊ ናቸው በሚባሉ ሸቀጦች ግዢ እና ሽያጭ ላይም እንደሚተገበር የጠቆሙት ደግሞ የኢትዮቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጽሚ ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ ናቸው።

የንግዱ ማኀበረሰብ ከቴሌብር ጋር ትሥሥር ከፈጸሙ 16 ባንኮች ደንበኛ ከሆኑበት ባንክ የአገልግሎት ክፍያቸውን መፈጸም ይችላሉ።

በሙሉጌታ በላይ
2022-10-24