
ረጅሙን የ እግር ኳስ ህይወቱን በማንቺስተር ዩናይትድ ቤት አሳልፏል ። ብዙዎች የማይረሱትን ግቦችም ከመረብ አሳርፏል ። የትላንቱ ተጫዋች የዛሬው አሰልጣኝ ዋይን ሮኒ ከዛሬ 37 ዓመት በፊት ጥቅምት 14 / 1985 በዛሬዋ ዕለት ተወለደ ። የዕለቱን ከታሪክ ትኩረታችን ነው።
የታላቁ ቡድን ማንቺስተር ዩናይትድ ባለውለታ ። ከ እንግሊዝ የ እግር ኳስ ኮኮቦች ተርታ ስሙ አብሮ የሚነሳ ። የኳስ አፍቃሪያን ዛሬም ድረስ ደጋግመው ቢያይዋቸው የማይጠግቡትን ድንቅ ጎሎች ለክለቡ ያስቆጠረ ፤ ጥበቦችን ያሳየ።
ተወዳጁ እንግሊዛዊ የፊት መስመር ተጫዋች ዋየን ማርክ ሮኒ ጥቅምት 14 /1985 በዛሬዋ ዕለት ወደዝች ምድር ተቀላቀለ ። ከልጅነቱ በኳስ ፍቅር የተጠመደው ሮኒ በዘጠኝ ዓመቱ የ ኤቨርተን አካዳሚን ተቀላቅሎ የእግር ኳስን ህይወቱን ሀ ብሎ ጀመረ ።
ዕድገቱና በየቀኑ የሚያሳያቸው ለውጦች ፈጣን ነበሩና በ 17 አመቱ በ ሞየስ ዋናው ቡድን ታየ ። ነገር ግን በዛ ቡድን ሊቆይ የቻለው ሁለት ዓመታትን ብቻ ነበር የወቅቱ ሀያላን ክለብ አይኖች ታዳጊው ልጅ ላይ አረፈ።
ሮኒን ለመውሰድ ቼልሲ ኒውካስትል እንዲሁም በርካታ ክለቦች ረብጣ ገንዘቦችን ማቅረብ ጀመሩ በመጨረሻም የማንቺስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ሰራሌክስ ፈርጉሰን ከ ቼልሲና ኒውካስተል የመሳሰሉ ክለቦች ጋር ተፋጠው መጪው ጊዜ ያማረ እንደሚሆን የተረዱትን ልጅ በ 25.6 ሚሊዮን ፓውንድ በ እጃቸው አስገቡት።
ይህ ልጅ የተለየ ብቃት አለው የሀገሪቱ ታላቅ ተጫዋች ለመሆንም ወደ ትክክለኛው ቦታ መቷል ሲሉም መሰከሩለት ። በወቅቱ ማንቺስተር ዩናይትድ የቀደመ ክብሩን በአርሴናል እየተነጠቀ ያለበት ሰዓት ነበርና ፈርጉሰን እንደነ ሮኒ ፤ ክርስቲያኖና ሌሎች አስደናቂ ብቃት ያላቸውን ልጆች ሰብስበው የራሳቸውን ጠንካራ ቡድን ማቋቋም ጀመሩ።
ሮኒ የሚያስቆጥራቸው ግቦች ፤አመቻችቶ የሚያቀብላቸው ኳሶች እንዲሁም ድንቅ የአጨራረስ ብቃቱ በቡድኑና በደጋፊዎቹ ተወደውለታል። ነገር ግን በአንድ ነገር ቅር ይሰኙበታል ሲበዛ እልሀኛ ነጭናጫና ሽንፈትን አምኖ መቀበል የሚከብደው በመሆኑ።
በሚያሳያቸው ያልተገቡ ባህሪዎች ዳኞች በተደጋጋሚ ቀይ ካርድ እንዲመዙ ያስገድዳቸዋል ። ይህ የሮኒ የተለየ ባህሪ ግን በአሰልጣኙ ፈርጉሰን ቦታ አልተሰጠውም ተወዳጁ አሰልጣኝ ከደጋፊዎች ትችት እየቀረበባቸውም ቢሆን ከሚያሳያቸው ያልተገቡ ባህሪያት ይልቅ የኳስ ጥበቡን ይበልጥ እንዲያድግ በመስራት ታዳጊውን ልጅ የቡድኑ መሪ አደረጉት ።
ሮኒም ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመሆን የማንቺስተርን የቀድሞ ክብር መለሰ ። ዩናይትድ ዋንጫ ተንበሸበሸ።
ስለሮኒ ተነስቶ ልትቀር የማትችል አንድ ነገር አለች ጊዜው 2011 ነው ከዛሬ 11 ዓመት በፊት በኦልትራፎርድ እየተደረገ ባለው የማቺስተር ደርቢ ዋይን ሮኒ ምን በወቅቱ ሊደግመው አይችልም የተባለለትን ጎል አስቆጠረ ።
የተሰጠውን ኳስ ከመሬት ከፍ ብሎ በመነሳት በመቀስ ምት ከመረብ አሳረፈ ። የሲቲ ደጋፊዎችን አንደበት የዘጋ ዩናይትዶችን በደስታ ያስነባ ሰራሌክስ ፈርጉሰንን እንዲዚህ አይነት ጎል አይቼ አላውቅም ያስባለ ክስተት ።
ዋይን ሮኒ አሁን 37ኛ አመቱ ላይ የሚገኝ ሲሆን የተጫዋችነት ጫማውን ሰቅሎ ደርቢ ካውንቲን በማሰልጠን ላይ ይገኛል ።
በዮሴፍ ከበደ
2022-10-24