ሀገሬ ቲቪ

በአፍሪካ የደኀንነት ሥጋት እየጨመረ መጥቷል

የሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር ዓለም አቀፉን የሠላምና የደኀንነት ጉባዔን እያስተናገደች ትገኛለች ትላንት የጀመረው ጉባዔ ዛሬም ተካሔዶ ውሏል። የተለያዩ ሀገራት ሚንስትሮች የድኀንነት ኃላፊዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተሳታፊ ነበሩ። አፍሪካ ለደኀንነቷ በርትታ ልትሰራ እንደሚገባ በዚህ ውይይት ተነስቷል።

የሴኔጋል ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ኀብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ማኪሳል ባደረጉት ንግግር አፍሪካ በተደጋጋሚ የምታነሳውን በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ም/ቤት እና በቡድን 20 ሀገራት ቋሚ መቀመጫ የማግኘቱ ጥያቄ ተቀባይነት እንደሚያገኝ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።

ማኪ ሳል ያነሱት አህጉሪቱ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ም/ቤት ቋሚ መቀመጫ የማግኘቱ ጥያቄ በሌሎች የጉባዔው ተሳታፊዎችም ሲስተጋባ እንደነበር አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል።

በአፈሪካ ኀብረት ለሴቶች እንዲሁም ሰላምና ደኀንነት ልዩ መለዕክተኛ የኾኑት ቢኔታ ዲኦፕ አፍሪካ እንደ አንድ ግዙፍ አህጉር በደኀንነቱ ካውንስል ጠረጼዛ ላይ ልትታይ ይገባታል ብለዋል።

አፍሪካ የራሷን ደህንነት በማስጠበቁ ረገድ ጥረት ማድረግ እንደሚገባት የፎረሙ ተሳታፊና የደኀንነት ኤክስፐርት የኾኑት ሞሐመድ ዝናጓኢ የተናገሩት

“አፍሪካ ለራሷ ደኀንነት ጥረት ማድረግ አለባት ስለአለም አንድነት ጥሪ ከማድረግ በፊት የአፍሪካ አንድነት ይቀድማል ከዚያ ነው። ከዚያ የአፍሪካ ቀዳሚ ሀብት የኾኑ ወጣቶቿን የማብቃት በጉዳዩ ማሰልጠን እንዲሁም የመንከባከብ ሥራ ይጠበቃል”

ባለፉት አስር ዓመታት በአፍሪካ በአማጺያን የሚደርሰው ጥቃት በመቶኛ ሲቀመጥ 300% እንደጨመረ የአሜሪካን የመከላከያ መሥሪያ ቤት ፔንታጎንን ሪፖርት ዋቢ አድርጎ ፕረስ ቲቪ ዘግቧል።

በአህጉሪቱ ምዕራብ ሳሀል እና ሶማሊያ ደግሞ አማጺዎች በሰፊው እንቅስቃሴ የሚያደርጉባቸው ቦታዎች መኾናቸውን ፔንታጎን አስታውቋል።

ትላንት እና ዛሬ በሴኔጋል ዳካር ሲካሔድ የቆየው የሰላም እና የደኀንነት ጉባዔ አህጉሪቱ በራሷ አቅም አሊያም በሌሎች ሀገራት ጥገና ስትኾን የደኀንነት አቅሟን ምታሳድግበት፣ የሕዝቦቿን የምግብ ፍላጎቷን ናየሀገራት ሉዓላዊነት የሚከበርበትን መፍትሔ ማበጀት ዋንኛ ዓላማው ነው።

በሙሉጌታ በላይ
2022-10-25