አትዮጵያ ስንዴን ወደ ውጪ ለመላክ ዝግጅት ላይ መኾኗን መንግሥት አስታውቋል። ለመኾኑ ይህ የልማት እንቅስቃሴ ምን ያህል ውጤታማ ነው፣ ያለውስ ዝግጅት ምን ይመስላል ስንል የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትን ጠይቀናል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ያናገርናቸው የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያ ጅማሬው መልካም መኾኑን ገልጽው መሻሻል ስላሉባቸው ጉዳዮችም ሀሳባቸውን ነግረውናል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ከፍተኛ የስንዴ ልማት ሥራዎች በመሰራታቸው ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት ስንዴ ወደ ኬንያ እንደምትልክም መንግሥት አስታውቋል። ይህ ዕቅድ እውን ይኾናል ወይ? የሀገር ውስጥ ፍላጎት በሚገባ ተሸፍኖ ነው ወደ ውጪ መላክ የታሰበው? የሚሉ እና ሌሎች ጥያቄዎችን በርካቶች ሲያነሱት ይስተዋላል።
እኛም ይህን ጥያቄ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የመስኖ ስንዴ ፕሮጀክት አስተባባሪ ለኾኑት ለዶ/ር ዳንዔል ሙለታ አቅርበናል።
በአብዛኛው በደጋማ አካባቢዎች ክረምትን እየተጠበቀ የሚዘራውን ስንዴ በበጋ እንዲዘራ መደረጉ እንዲሁም መስኖን በመጠቀም በቆላማ አካባቢዎችም እንዲለማ የማድረጉ ሥራ ስኬታማ መኾኑ ሀገሪቱ ከራሷ አልፎ ወደ ውጪ መላክ የሚያስችላት ነው ብለውናል።
በዘንድሮ ዓመት ምንም እንኳን 1 ሚሊዮን ሔክታሩ በኦሮሚያ ክልል የሚለማ ቢኾንም ይህ የመስኖ ስንዴን በ 9 ክልሎች እንዲሰፋ መደረጉን ዶ/ር ዳንዔል ተናግረዋል።
በአፋር ክልል 30 ሺ ሄክታር በአማራ ክልል 250ሺህ ሄክታር እንዲለማ እየተደረገ ነው ብለዋል። በጋንቤላ ክልል የመጀመሪያ እንደመኾኑ በ 500 ሔክታር ላይ ስንዴ እንዲለማ እየተደረገ ነው።
አገሪቱ በአጠቃላይበ 1.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት 153 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማምረት ውጥን ይዛለች ይህ ስኬታማ እንዲኾን በተጀመረው የስንዴ ልማት ላይ በመስኖ ሥራ ላይ መሻሻል የሚገባቸው ሥራዎች እንዳሉ የግብርና ኢኮኖሚስቱ ደምስ ጫንያለው(ዶ/ር ) ተናግረዋል።
የመስኖ ስንዴ በውናነት ገበሬው የእርሻ መሬቱን አንድ ላይ በማቀናጀት በኩታገጠም ዘዴ ነው እንዲያመርት እየተደረገ ያለው ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) ይህ አሰራር በግብርናው ዘርፍ መሠረታዊ ለውጥ አይሰጥም ሲሉ ገልጸዋል።
በቀጣይ የግብርና ሚኒስቴር ወደ 10 የሚጠጉ የቅባት እህሎች ምርትን የማስፋት ውጥን እንዳለው ሰምተናል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-10-26
